የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ በ22 የመንገድና ስትራክቸር ግንባታ ፕሮጀክቶች የግንባታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ በበጀት አመቱ በ39 የመንገድና ስትራክቸር ግንባታ ፕሮጀክቶች አማካኝነት 93.01 ኪ.ሜ መንገድ እና በርካታ ስትራክቸሮች ለመገንባት አቅዶ የነበረ ቢሆንም በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት በሁሉም ፕሮጀክቶች ስራ መጀመር ባለመቻሉ አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው የጎንደር፣ ወሎና ሰሜን ሸዋ ክላስተሮች በሚገኙ 22 የመንገድና ስትራክቸር ግንባታ ፕሮጀክቶች ከታህሳስ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ የግንባታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ኤጀንሲው ወደ ስራ ከገባባቸው 22 ፕሮጀክቶች መካከል የመንገድ ግንባታ ስራ በሚያከናውኑ 14 ፕሮጀክቶች በበጀት አመቱ በድምሩ 46.63 ኪ.ሜ በ8 ወሩ ደግሞ 23.87 ኪ.ሜ መንገድ ለመገንባት አቅዶ ወደ ስራ የገባ ሲሆን እስከ የካቲት መጨረሻ 2016 ዓ.ም ባለዉ ጊዜ 11.48 ኪ.ሜ መንገድ በመገንባት የ8 ወሩ እቅድ 48.12% የአመቱን ዕቅድ ደግሞ 24.63% ፈጽሟል።
ኤጀንሲው ወደ ስራ ከገባባቸዉ ፕሮጀክቶች መካከል በ8 የስትራክቸር እና በ4 የመንገድ ግንባታ በድምሩ በ12 ፕሮጀክቶች አማካኝነት 45 የአነስተኛ፣ መካከለኛ እና ትላልቅ ስትራክቸሮች ግንባታ የሚያከናውን ሲሆን በእነዚህ ፕሮጀክቶች እስከ የካቲት ወር መጨረሻ 2016 ዓም ድረስ በተከናወነዉ የግንባታስራ የ8 ወሩ እቅድ 26.68% የአመቱን ዕቅድ ደግሞ 16.10% ማከናወን ተችሏል።
ኤጀንሲው በቀጣይም በጎጃም ክላስተር የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ለማስገባት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛሉ።





