የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ አመሰራረት
የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ባለፉት 30 ዓመታት ከ6 ሽህ ኪ.ሜ በላይ የመንገዶች ግንባታ አከናወነ፡፡
የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት
ከአምባ ጊዮርጊስ እስከ ስላሬ የሚዘልቀው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው። በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ ከአምባ ጊዮርጊስ እስከ ስላሬ የሚዘልቀው እና 50 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የጠጠር መንገድ ፕሮጀክት በክልሉ መንግሥት በጀት እና በመንገድ ቢሮ ባለቤትነት እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት ነው። በአማራ ክልል የገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ የሚገነባው ፕሮጀክቱ በተያዘው በጀት ዓመት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲኾን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። የመንገድ ፕሮጀክቱ መገንባት የአምባ ጊዮርጊስ ከተማን እና የወገራ ወረዳ ቀበሌዎችን ከስላሬ ከተማ እንዲሁም ኪንፋዝ በገላን የሚያገናኝ ሲኾን ከ13 በላይ ቀበሌዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተነግሯል። እንደ ከክልሉ መንገድ ኤጀንሲ መረጃ ለፕሮጀክቱ ሥራ የአካባቢው ማኅበረሰብ ክትትል፣ ድጋፍ እና ትብብር ምስጋና የሚገባው መኾኑ ተጠቁሟል። በቀጣይም ለሥራው መጠናቀቅ ተገቢውን እገዛ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ተመላክቷል። ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ኮሙኒኬሽን የመረጃ መረቦች ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ይችላሉ፡፡ በበጀት ዓመቱ ወደ ሥራ መግባት ከነበረባቸዉ 39 ፕሮጀክቶች መካከል 36 የመንገድ እና ድልድይ ግንባታ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገብተዉ የግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ፡፡
የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ በበጀት ዓመቱ ከክልሉ መንግስት በተመደበ ብር 1.1 ቢሊዮን /አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን/ ብር በጀት በ39 የመንገድና ድልድይ ፕሮጀክቶች 80 ኪ.ሜ መንገድ እና 78 የተለያየ መጠን ያላቸዉ ድልድዮች ግንባታ ለማከናወን አቅዶ እየሰራ ይገኛል፡፡ የ2017 ዓ.ም የፕሮጀክቶች በጀት በወቅቱ ባለመለቀቁ ምክንያት ፕሮጀክቶች ዘግይተዉ ሥራ የጀመሩ ሲሆን እስከ የካቲት መጨረሻ 2017 ዓ.ም ድረስ ባለዉ ጊዜ ከ39 ፕሮጀክቶች መካከል 36 ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገብተዉ ዕቅዶቻቸዉን ለመፈፀም የመንገድ እና የተለያየ መጠን ያላቸዉ ድልድዮች ግንባታ እያከናወኑ ይገኛሉ ፡፡ ቀሪ 3 /ሦስት / ፕሮጀክቶች በአካባቢዉ በሚስተዋለዉ ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ምክንያት እስከ የካቲት መጨረሻ 2017 ዓ.ም ድረስ ባለዉ ጊዜ ወደ ሥራ መግባት አልቻሉም ፡፡ ወደ ግንባታ ሥራ ያልገቡ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ባለፉት 8 ወራት 3‚459.91 ኪ.ሜ የነባር መንገዶች ጥገና አከናወነ።
የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ በ2017 ዓ.ም ከፌዴራል መንገድ ፈንድ ጽ/ቤት በተመደበለት ብር 975 ሚሊዮን 546 ሺህ ስልሳ ሁለት ብር በጀት በ6 ጥገና ጽ/ቤቶች (ጎጃም፣ ጎንደር፣ ደብረታቦር፣ ወልዲያ፣ ደሴ እና ሰሜን ሸዋ) 5‚481.97 ኪ.ሜ መንገድ ለመጠገን አቅዶ እስከ የካቲት 30/2017 ዓ.ም ድረስ ባሉት 8 ወራት ባካሄደው የስራ እንቅስቃሴ 3‚459.91 ኪ.ሜ ነባር መንገዶችን በመጠገን የአመቱን እቅድ 63.11% አከናውኗል።ኤጀንሲው ባለፉት 8 ወራት ካከናወነው 3‚459.91 ኪ.ሜ ውስጥ 358.45 ኪ.ሜ (10.36%) በወቅታዊ የጥገና ስልት የተጠገነ ሲሆን 3,101.46 ኪ.ሜ (89.64%) የሚሆነዉ በመደበኛ የጥገና ስልት የተጠገነ ነው። ባለፉት 8 ወራት ከተከናወነው 3,459.91 ኪሜ የጥገና ሥራ መካከል 1,949.24 ኪ.ሜ (56.34%) የሚሆነዉ በመሣሪያ ኃይል የተጠገነ ሲሆን ቀሪው 1‚510.67 ኪ.ሜ (43.66%) የሚሆነዉ ደግሞ በሰው ሀይል የተጠገነ ነው።ኤጀንሲው የበጀት አመቱን የጥገና እቅድ በ257 የጥገና መስመሮች የሚያከናውን ሲሆን ከእነዚህ መካከል በ185 መስመሮች የሚያከናውነውን ጥገና ሙሉ በሙሉ አጠናቋል።
አለም አቀፍ የሴቶች ቀን
የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ እና የመንገድ ቢሮ ሴት ሰራተኞች አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በፓናል ውይይት አከበሩ።
የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲና የመንገድ ቢሮ ሴት ሰራተኞች ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል በሚል መሪ ቃል አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በፓናል ውይይት አክብረዋል።
በፓናል ውይይቱ እንደተገለፀው በዚህ አመት የሚከበረው የሴቶች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ49ኛ ጊዜ በክልል ደረጃ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ እንደሚከበርና ሞዴል የሴቶች የልማት ህብረቶችን ማጠናከር፣ ሴቶች የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ በንቅናቄ እንዲቆጥቡ ማድረግ፣ በግብርናና በኢንዱስትሪ መስክ ተሰማርተው የሚገኙ ሴቶች ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ ማድረግ፣ ሴቶች የማህፀን በርና የጡት ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ በማድረግና ቦንድ በመግዛት ለህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ማድረግ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።
በውይይቱም ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት በጋራ ሰብሰብ ብሎ መደራጀትና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል ማዳበር እንደሚገባቸው ተገልጿል።
በውይይቱም የክልሉ መንገድ ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ጋሻው አወቀ፣ የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ፣ የገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቀለሙ ሙሉነህ እና ሌሎች የመንገድ ቢሮ እና የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ አመራሮች ተገኝተዋል።