‹‹የአማራ ገጠር መንገዶች ድርጅት›› በሚል ስያሜ ጥቅምት 1987 ዓ.ም ራሱን ችሎ በአዋጅ ተቋቋመ፡፡

 
መንገድ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ልማት ወሳኝ የመሰረተ ልማት ዘርፍ መሆኑን በመገንዘብ የህብረተሰቡን የመንገድ ተደራሽነት ፍላጐት ሊመልስ የሚችል ጠንካራ ተቋም ለማድረግ በማሰብ ከተቋቋመ ከአንድ ዓመት በኋላ ጥቅምት 3/1988 ዓ.ም ‹‹የአማራ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን›› በሚል ስያሜ እንደገና በአዋጅ ቁጥር7/1988 ዓ.ም ማሻሻያ ተደርጐለት በባለስልጣን ደረጃ ተቋቋመ፡፡

ይህን ስያሜ ይዞ እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ለ20 ዓመታት የመንገድ/ድልድይ ግንባታ እና ጥገና እንዲሁም የኮንትራት አስተዳደር ስራዎችን ሲያከናውን ነበር፡፡ ኤጀንሲዉ በባለስልጣን ደረጃ የተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር7/1988 ዓ.ም በ1991፣በ1995 እና በ2005 ዓ.ም ወቅቱ የሚጠይቃቸዉ የአዋጅ ማሻሻያዎች ተካተዉበት አዋጁ እንደገና ተሻሽሎ በመፅደቅ ሲሰራበት የቆየ ሲሆን ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ከኮንትራት አስተዳደር ስራዎች ወጥቶ ‹‹የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ›› በሚል ስያሜ የመንገድ እና ድልድይ ግንባታና ጥገና ስራዎችን የሚያከናውን ተቋም ሆኖ በመደራጀት ተግባርና ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡
ኤጀንሲው በቀጣይ ከሚመለከታቸዉ አጋር አካላት ጋር ተባብሮ በመስራት የክልሉን ህብረተሰብ የመንገድ ተደራሽነት ጥያቄ ለመመለስ እና በክልሉ በመንገድ እና ድልድይ ግንባታና ጥገና ዘርፍ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ ተቋም ለመሆን አልሞ እየሰራ ይገኛል፡፡