የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታችን ወጪ ቆጣቢ፣ ጥራት ያለውና ረጅም ግልጋሎት እንዲሰጥ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

የመንገድ ልማት ሥራ በኪሎ ሜትር ብዛት ብቻ የሚለካ ሳይሆን በጥራቱ፣ በዘላቂነቱ እና ለህብረተሰቡ በሚያመጣው አገልግሎት የሚመዘን ነው።

ጥራት ያለው መንገድ የጉዞ ጊዜን ያሳጥራል፣ የተሸከርካሪና የመለዋወጫ ወጪን ይቀንሳል፣ የትራንስፖርት ደህንነትን ያረጋግጣል፣ እንዲሁም የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ያጠናክራል።

የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ በክልሉ የሚገነቡና የሚጠገኑ መንገዶች እና ድልድዮች የተፈለገውን የጥራት ደረጃ እንዲያሟሉ በመድረግ እየሰራ ይገኛል።

በተለይም አስቸጋሪ የተራራማ መሬት አቀማመጥን በኢንጂነሪንግ ጥበብ በማሸነፍ የሚገነቡ መንገዶች የባለሙያዎችን ክህሎት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የልማት ቁርጠኝነት ያንጸባርቃሉ።

በክልሉ በተራራማና ፈታኝ የቶፖግራፊ ሁኔታዎች ውስጥ ሳይቀር ተራራዎችን በመቁረጥ፣ ገደሎችን በማለፍ እና የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ የመንገድ እየተገነባ ይገኛል።

በዚህም ኤጀንሲው የተፈጥሮ እንቅፋቶችን ወደ ልማት እድሎች በመቀየር ህብረተሰቡን ከገበያ፣ ከትምህርት፣ ከጤና እና ከሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ጋር በማስተሳሰር ለክልሉ ዘላቂ እድገት መሰረት ለመጣል በከፍተኛ ትጋት በመስራት ላይ ነው።

ኤጀንሲው በየዓመቱ በስድስቱ የጥገና ጽ/ቤቶች በሚከናወኑ የመንገድና የድልድይ ፕሮጀክቶች ላይ የጥራት ቁጥጥርና ክትትል ስራዎችን በስፋት ያከናውናል።

በተጨማሪም በፕሮጀክቶች፣ በኳሪ ሳይቶች እና በግንባታ ግብዓቶች ላይ የጥራት ምርመራና ክትትል በማካሄድ የግንባታ ሥራዎች በተቀመጠው መስፈርት መሰረት እንዲከናወኑ ያደርጋል።

የመንገድ ሀብት አስተዳደርን ለማዘመን የተጠናቀቁ መንገዶችን እና ድልድዮችን በዲጂታል ስርዓት በመመዝገብ ወደ ዳታቤዝ ያስገባል። ይህም የመንገድ ሀብት መረጃዎችን በተደራጀ መልኩ ለማስተዳደርና ለውሳኔ አሰጣጥ ለመጠቀም አስፈላጊ መሰረት ይፈጥራል።

በተጨማሪም የመንገድና የድልድይ ፕሮጀክቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ የመንገድ መስመሮች መረጃ ማጥራት፣ የመንገድ ሁኔታ ጥናት፣ የድልድዮችና የሌሎች ስትራክቸሮች መረጃ መሰብሰብና ማደራጀት በዘመናዊ አሰራር ያከናውናል።

ኤጀንሲው ፕሮጀክቶችን በጥራት፣ በቅልጥፍና እና በተጠያቂነት በማስፈጸም የሚገነቡት መንዶችና ድልድዮች ለረጅም ዘመናት አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረግ አኳያ የግብዓትና የግንባታ ቁጥጥር ስርዓት በመዘርጋት ለክልሉ ዘላቂ ልማት መሰረት የሆነ የመንገድ መረብ ለመገንባት ቁርጠኛ ሆኖ እየሰራ መሆኑን ሲገልጽ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ነው።                                                      

ወጭ ቆጣቢ፣ ጥራትና ረጅም አገልግሎት የመንገድ ግንባታ ስራዎቻችን መለያዎች ናቸው፡፡