የአማራ ገጠር መንገደች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋናው መ/ቤት አመራሮች እና ሰራተኞች በኤጀንሲው የ2018 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ውይይት አካሄዱ።

የኤጀንሲው የ2018 ዓ.ም የቁልፍ እና ዓበይት ተግባራት ዓላማዎችና ግቦች እንዲሁም ዝርዝር ተግባራትን ያካተተ የመንገድ ልማት ስራዎች እቅድ በ04/13/2017 ዓ.ም በኤጀንሲው የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትል እና ግምገማ ደጋፊ የሥራ ሂደት መሪ አቶ ባሻ እንግዳው ቀርቦ በኤጀንሲው ዋና መ/ቤት አመራሮች እና ሠራተኞች ውይይት ተደርጎበታል።


  


እቅዱ በቀረበበት ወቅት ኤጀንሲው በ2018 በጀት አመት ከክልሉ መንግስት በተመደበ ከብር 1.3 ቢሊዮን በላይ በጀት በ33 ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶች 102.15 ኪ.ሜ መንገድና 227 ስትራክቸሮችን ለመገንባት እና ከፌዴራል መንገድ ፈንድ ጽ/ቤት በተመደበ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በ289 የጥገና መስመሮች 6‚038 ኪ.ሜ ነባር መንገዶችን ለመጠገን በእቅድ መያዙ ተገልጿል።

በውይይቱም የተቋሙ እቅድ ክልሉ ካቀደው የ25 አመት የአሻጋሪ እድገትና ዘላቂ ልማት ፍኖተ ካርታ ከተወሰደ የ5 አመታት ስትራቴጅክ እቅድ መነሻ ተደርጎና የህዝብን የመልማት ጥያቄ ግምት ውስጥ አስገብቶ የተዘጋጀ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራር ወጣ ባለ መልኩ መፈፀምን የሚጠይቅና የሁሉንም አካል የጋራ ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑ በተቋሙ ሰራተኞች ዘንድ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

 

የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቀለሙ ሙሉነህ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንደገለፁት ኤጀንሲው የመንግስትና የህዝብን ተልዕኮ የተሸከመ ተቋም በመሆኑ ከእያንዳንዳችን ምን ይጠበቃል የሚለውን በአግባቡ ይዞ መስራት የሚጠበቅ ሲሆን እቅድን፣ ሀብትንና የሰው ሃይልን በጥብቅ ዲሲፕሊን መምራት ከአመራሩ እንደሚጠበቅና ሰራተኛውም የእቅዱ ባለቤት መሆን፣ የታቀደውን እቅድ ለመፈፀም ቁርጠኛና ተነሳሽ መሆንና ስራን በጋራ፣ በቅልጥፍናና በቅንነት በመስራት እቅዱን ማሳካት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።