የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለመፈፀም ጥረት በማድረግ ላይ ነዉ፡፡
ኤጀንሲዉ በበጀት ዓመቱ ከክልሉ መንግስት በተመደበ 1.1/አንድ ነጥብ አንድ/ ቢሊዮን ብር ካፒታል በጀት በ39 የመንገድና ድልድይ ፕሮጀክቶች 80 ኪ.ሜ መንገድ እና 88 የተለያየ መጠን ያላቸዉ ስትራክቸሮች ግንባታ ለማከናወን አቅዶ እየሰራ ሲሆን እስከ መጋቢት መጨረሻ 2017 ዓ.ም ባለዉ ጊዜ ወደ ስራ በገባባቸዉ 36 የመንገድና ድልድይ ፕሮጀክቶች 17.37 ኪሜ የመንገድ ግንባታ በማከናወን የ9 ወሩን ዕቅድ 38.84% ፣የዓመቱን ዕቅድ ደግሞ 21.72% አከናዉኗል፡፡ ኤጀንሲዉ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለመፈፀም ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆን ባለፉት 9 ወራት የተለያየ መጠን ያላቸዉ ድልድዮች በመገንባት ረገድ የተሻለ አፈፃፀም ታይቷል፡፡ የ9 ወሩ የመንገዶች ግንባታ አፈፃፀም ግን አነስተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ በመንገዶች ግንባታ የተመዘገበዉ አነስተኛ አፈፃፀምም ቢሆን ፈተናዎችን ተቋቁሞ በመስራት የተመዘገበ አፈፃፀም ነዉ ፡፡
ለአፈፃፀሙ ማነስ በክልሉ በተፈጠረዉ የፀጥታ ችግር ምክንያት በሙሉ አቅም መስራት አለመቻል፣ የራስ ኃይል የግንባታ ማሽነሪ እና ተሸከርካሪ እጥረት፣የኪራይ ማሽነሪ እና ተሸከርካሪ እንዲሁም መለዋወጫ በገበያ ላይ ማግኘት አለመቻል በዋናነት ይጠቀሳሉ ::
በቀሪ ወራት በፈተና ዉስጥ ሆኖም ቢሆን የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ሰፊ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ የኤጀንሲዉ የ2017 ዓ.ም የ9 ወር ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ከኤጀንሲዉ ዋና መ/ቤት አመራሮች እና ሰራተኞች ጋር በተካሄደበት ወቅት ተመልክቷል፡፡