አለም አቀፍ የሴቶች ቀን

የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ እና የመንገድ ቢሮ ሴት ሰራተኞች አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በፓናል ውይይት አከበሩ።

የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲና የመንገድ ቢሮ ሴት ሰራተኞች ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል በሚል መሪ ቃል አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በፓናል ውይይት አክብረዋል።

 

በፓናል ውይይቱ እንደተገለፀው በዚህ አመት የሚከበረው የሴቶች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ49ኛ ጊዜ በክልል ደረጃ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ እንደሚከበርና ሞዴል የሴቶች የልማት ህብረቶችን ማጠናከር፣ ሴቶች የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ በንቅናቄ እንዲቆጥቡ ማድረግ፣ በግብርናና በኢንዱስትሪ መስክ ተሰማርተው የሚገኙ ሴቶች ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ ማድረግ፣ ሴቶች የማህፀን በርና የጡት ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ በማድረግና ቦንድ በመግዛት ለህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ማድረግ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።

በውይይቱም ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት በጋራ ሰብሰብ ብሎ መደራጀትና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል ማዳበር እንደሚገባቸው ተገልጿል።

በውይይቱም የክልሉ መንገድ ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ጋሻው አወቀ፣ የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ፣ የገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቀለሙ ሙሉነህ እና ሌሎች የመንገድ ቢሮ እና የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ አመራሮች ተገኝተዋል።